በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ18 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተመረቀ

ሐምሌ 25/2014 (ዋልታ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ኩርሙክ ወረዳ ዱል ሆዴ ቀበሌ ለሚገኙ ነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና በክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተመርቋል።
የውኃ ፕሮጀክቱ 5 ሺሕ 800 ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት እንደሚሰጥ እና ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት የክልሉ ውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙፍቲ መርቀኒ ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን የክልሉ መንግሥት የዜጎችን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸው በንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የደስታ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኩርሙክ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ እስማኤል አብዱራህማን በውኃ ተቋሙ የግንባታ ሥራ ውጤታማነት አስተዋፅኦ ያበረከቱ አካላትን ማመስገናቸውን ኢብኮ ዘግቧል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ በፊት በንፁህ የመጠጥ ውኃ እጥረት ከፍተኛ እንግልት ሲደርስባቸው እንደነበር ገልጸው በውኃ ፕሮጀክቱ መመረቅ መደሰታቸውን ገልጸዋል።