ኢመደአ እና አዋሽ ባንክ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

ሐምሌ 26/2014 (ዋልታ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ፒኤችዲ) እና የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጸሃይ ሺፈራው ፈርመውታል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ኢመደአ የአገሪቱን የሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ ለሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ ሥራዎች የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ በአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የተደረገ ሲሆን፤ በሌላም በኩል የባንኩን የኢንፎርሜሽንና ኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማት ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ድጋፍና እገዛ በኢመደአ በኩል ይሰጣል፡፡

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተሩ በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት ጠንካራ ሃገር መገንባት የሚቻለው ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ሲቻል ነው ብለዋል፡፡
ኢመደአ የአገራችንን የሳይበር ደህንነት የማስጠበቅ ዋና ተልዕኮውን ለማሳካት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ ይሰራል ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ ከአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር የተደረገው የጋራ መግባቢያ ስምምነት ፊርማም የአስተዳደሩ የትብብርና የቅንጅት ሥራ አንዱ አካል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው ኢመደአ የፋይናንስ ሴክተሩን ጨምሮ ቁልፍ የሃገራችንን ተቋማት የሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ የሚሰራቸው ሥራዎች ከፍተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ ለኢመደአ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የሁለቱ ተቋማት የትብብርና የቅንጅት ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ያመላክታል፡፡