የኢትዮጵያና ቻይና አቻ ኢንስቲትዩቶች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ሐምሌ 26/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እና የቻይና ሕዝብ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩቶች በጋራ ለመስራት ተስማሙ፡፡

የኢንስቲትዩቶቹ ተወካዮች በሚሲዮኑ አስተባባሪነት የበይነመረብ ውይይት ማካሄዳቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ቻይና እና ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸው እ.ኤ.አ በ2017 ግንኙነታቸው ወደ ሁሉን-ዐቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር ደረጃ ማደጉን ተናግረዋል።

አክለውም ባሳለፍነው ዓመት በሴኔጋል ርዕሰ መዲና ዳካር የተካሄደው 8ኛው የአፍሪካ ቻይና ትብብር ፎረም የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ካስቀመጣቸው ዘጠኝ ዋና ዋና የትብብር መስኮች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አንደኛው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሁለቱ አቻ ተቋማት በተለይም በጋራ የምርምር ሥራዎች፣ በመረጃ፣ ህትመትና ልምድ ልውውጥ እንዲሁም የጋራ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ተባብረው እንዲሰሩና ግንኙነታቸውን የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ኤክስኪውቲቭ ዳይሬክተር ደሳለኝ አምባው (ፒኤችዲ) ሁለቱ ተቋማት የካበተ ልምድ ያላቸው ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ  የሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትልቅ አቅም አላቸው ብለዋል፡፡

ከቻይናው አቻ ተቋም ጋር አምባሳደሩ በጠቀሷቸው የትብብር መስኮች ዙሪያ ተባብሮ ለመስራት ፅኑ ፍላጎት ያላቸውና ለዚህም ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የቻይና ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሊ ዢ  ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ሥፍራ የምትሰጥ መሆኑንና ቻይና ከአፍሪካ ጋር ለምታደርገው ትብብር ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና ያላት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተቋማቸው በቀረቡት የትብብር መስኮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።