የአፋር ክልል ም/ቤት የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

ሐምሌ 26/2014 (ዋልታ) የአፋር ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቋል።

ጉባኤው የክልሉን የአስፈጻሚ አካላትን ተግባርና ኃላፊነት እንደገና ለማደራጀት የተዘጋ ረቂቅ አዋጅ በክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ፋጡማ መሀመድ ለምክር ቤቱ በንባብ ቀርቧል።

ምክር ቤቱም የቀረበው የአስፈጻሚ አካላት ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ላይ ውይይት በማድረግ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

በዚሁ መሰረት እንደ አዲስ ለተዋቀሩት ሶስት ቢሮዎች የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተሿሚዎችን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

ምክር ቤቱም አሊ ባሂና አሊ የክልሉ ማዕድን ሀብት ቢሮ ኃላፊ፣ ወላህ ውቲካ የክልሉ የተፋሰስ ልማት ቢሮ ኃላፊ እና ሃሚድ ዱላ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ እንዲሆኑ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ያቀረቡትን ሹመት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

በተጨማሪም የአፋር ክልል ምክር ቤት በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቅራቢነት 34 የወረዳ እና 5 የዞን ፍርድ ቤት ፕሬዚዳቶችን ሹመት መርምሮ በማጽደቅ ጉባኤውን አጠናቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።