አሜሪካ የዝንጀሮ ፈንጣጣ የኅብረተሰብ የጤና ስጋት ነው ስትል አወጀች

የዝንጀሮ ፈንጣጣ

ሐምሌ 29/2014 (ዋልታ) በአሜሪካ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ የአገሪቱ መንግሥት በሽታው የኅብረተሰብ የጤና ስጋት ነው ሲል አወጀ።

መንግሥት በሽታው የኅብረተሰብ ጤና ስጋት ነው ብሎ ማወጁ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የክትባት ስርጭት እንዲስፋፋ፣ ሕክምና እና የፌዴራል መንግሥት ሃብት እንዲጨምር ያደርጋል ተብሏል።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ የተሰማው የዓለም ጤና ድርጅት ከሁለት ሳምንት በፊት በሽታው የዓለም ሕዝብ የጤና ስጋት ነው ብሎ ካወጀ በኋላ ነው።

እስካሁን በአሜሪካ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ6 ሺሕ 600 መሻገሩን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከል አንድ አራተኛው በአሜሪካዋ ኒው ዮርክ የተመዘገበ ሲሆን ካሊፎርኒያ እና ኢሊኖይስ ከኒው ዮርክ በመቀጠል በርካታ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መገኛ ግዛቶች ሆነዋል።

ከአውሮፓውያኑ 2020 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በመላው ዓለም በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ከ26 ሺሕ በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከል (ሲዲሲ) አሐዝ ያሳያል።

በዝንጀሮ ፈንጣጣ የትኛውም ሰው ሊይዝ የሚችል ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በበሽታው በብዛት እየተያዙ ያሉት በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ወንዶች መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አንዳንድ የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎች በሽታው ‘የኅብረተሰብ ጤና ስጋት’ ተብሎ መታወጁ በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ሊያገል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በቀጥታ በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ኢንፌክሽን ባይሆንም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ማድረግ በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል።