ሚኒስቴሩ የሽግግር ሂደቱ ለ2 ዓመታት መራዘም የደቡብ ሱዳናዊያንን ጥቅም እስካስጠበቀ ድረስ የሚደገፍ ውሳኔ ነው አሉ

ሐምሌ 29/2014 (ዋልታ) የደቡብ ሱዳን መንግሥት የተጀመረውን የሰላማዊ ውይይት በውጤታማነት ለማከናወን እንዲቻል የምርጫ ሰሌዳውን ለሁለት ዓመታት ማራዘሙ የደቡብ ሱዳናዊያንን ጥቅም እና ፍላጎት ግምት ውስጥ እስካስገባ ድረስ የሚደገፍ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ባወጣው መግለጫ የደቡብ ሱዳን መንግሥት የተጀመረውን ሰላማዊ ውይይት በተሳካ መልኩ ለማከናወን የምርጫ ግዜውን በሁለት ዓመታት ለማራዘም ውሳኔ ማሳለፉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት እስካግባባና የደቡብ ሱዳናዊያንን ጥቅም እስካስጠበቀ ድረስ ውሳኔውን በአዎንታ እንደሚመለከተው አስታውቋል።

ውሳኔው አሁን ላይ ደቡብ ሱዳን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ያስገባ ብሎም ሁሉንም ደቡብ ሱዳናዊያን ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የተወሰነ ሆኖ ከተገኘ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑንም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ደቡብ ሱዳናዊያን አሁን በጀመሩት መልኩ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ጥበብ የሚቀጥሉ ከሆነ የተቀመጠውን የሽግግር ሂደት ውጤታማ ሊያደርጉ እንደሚችሉም እምነት እንዳለው ጠቅሷል።

ደቡብ ሱዳን ሰላማዊ ሽግግሩን በውጤታማ መልኩ እስክታሳካ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ልክ እንደ እስከዛሬው ሁሉ ከወንድም የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ጎን እንደሚቆም ገልጿል።

ደቡብ ሱዳናዊያን የተረጋጋ ሰላም እና ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ድጋፍ እንደማይለያቸውም ማስታወቁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።