በኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎች የጎርፍ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተገለጸ

ሐምሌ 3/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ 1 ሚሊዮን 728 ሺሕ 407 ዜጎች የጎርፍ አደጋ እንደተጋረጠባቸውና ከእነዚህም ውስጥ ከ407 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቀዬአቸው እንደሚፈናቀሉ ተገምቷል፡፡

በቀጣዮቹ የክረምት ወራትም ከመደበኛው ከፍ ያለ ዝናብ በወንዝ ተፋሰሶች አካባቢ አዳጋ ሊያስከተትል ይችላል ነው የተባለው፡፡

በዚህም በተከዜ፣ አባይ፣ አዋሽ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ባሮ እና አኮቦ ወንዞች እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ተብሏል፡፡

የቆጋ እንዲሁም ርብ ግድቦችና የጣና ሀይቅም የመሙላት አደጋ የተደቀነባቸውና አስቸኳይ ስራን የሚፈልጉ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡

የፓስፊክ ውቅያኖስ ምስራቃዊና መካከለኛ ክፍሎች ላይ የሚገኙ የውሃ አካላት መሞቅና መቀዝቀዝ የሚፈጥረው የአየር ሁኔታ ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ የሜቲዎሮሎጂ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

የፓስፊክ ውቅያኖስ ከመደበኛው በላይ መቀዝቀዝ ያስከተለው “ላ ኒና” የተሰኘ ተፅዕኖ በኢትዮጵያ በዘንድሮው የክረምት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ አስከትሏል፡፡

በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋርና ጋምቤላ ክልሎችም ዝናቡን ተከትሎ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ተከስቷል፡፡

በቀሪ የክረምት ወራት የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራዎችን ለመስራት ከብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲቲዩት፣ ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ ከክልሎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ ጠቅሰዋል፡፡

የቀሪ የክረምት ወራት ቅድመ ማስጠንቀቂያና የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት ተካሂዷል፡፡

ሳሙዔል ሓጎስ (ከቢሾፍቱ)