በአልሸባብ የሽብር ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረ ተቀጣጣይ ፈንጂ ተያዘ

ነሐሴ 3/2014 (ዋልታ) በአልሸባብ የሽብር ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረ ተቀጣጣይ ፈንጅ የጫነ ተሽከርካሪ ከነአጥፍቶ ጠፊዎቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

የኮማንድ ፖስቱ አባልና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል መሐመድ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት በድንበር አካባቢ በነበረው ጥብቅ ፍተሻ በአልሸባብ የሽብር ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረ ተቀጣጣይ ፈንጅ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን የጫነው ተሽከርካሪም ከነአጥፍቶ ጠፊዎቹ በሶማሊያ የጠረፍ ከተማ ጉልዶጎብ አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ቦህ ወረዳ ሊገባ ሲል ነው የተያዘው።

በቁጥጥር ስር የዋለው ተሽከርካሪ የሀብሀብ ፍራ ፍሬ የጫነ መስሎ ሊያልፍ ሲሞክር በኢትዮጵያና በሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች ጥምረት በተደረገው ፍተሻ ፈንጂ ጭኖ መገኘቱን ነው የተናገሩት።

የተያዘው ፈንጂ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደረስ እንዲሁም በህንጻዎችና በመንገዶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ሊያደርስ የሚችል መሆኑን ኮሚሽነር ጄነራሉ ገልጸዋል።