በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለው ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ

ነሐሴ 3/2014 (ዋልታ) በምስራቅ ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለው ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉን በቀጣናው የሚገኘው የክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ገለፁ።

በምስራቅ ወለጋ ዞን በጊዳ አያና፣ ኪረሙ፣ በኢበንቱ፣ በሀሮሊው እና በሊሙ ወረዳዎች ዙሪያና አካባቢው በአሸባሪው የሸኔ ታጣቂ ቡድን ላይ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ እየተወሰደበት እንዳለ ተገልጿል።

በግዳጅ ቀጣና የሚገኘው የክፍለ ጦር ዋና አዛዥ እንዳሉት በአሸባሪው የሕወሓት ሳንባ በሚተነፍሰው የሸኔ ታጣቂ ቡድን ላይ በተወሰደው የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ 49 የሸኔ ታጣቂ ቡድን አባላት ሲማረኩ፣ አምስቱ እርምጃ ተውስዶባቸዋል፤ 50 የሚሆኑት ጀሌዎች ደግሞ ለሽብር ቡድኑ መረጃ ሲያቀብሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በዚህ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ አሸባሪው ሸኔ ከሕዝብና ከመንግሥት ተቋማት ዘርፎ ሲጠቀምባቸው የነበሩ 18 ሞተር ሳይክሎች፣ 44 ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ 26 ልዩ ልዩ መሳሪያዎች፣ 25 በርሜል ነዳጅን ጨምሮ 74 ሺሕ 795 ብር መያዙን ተናግረዋል።

ዋና አዛዡ አክለውም ክፍለ ጦሩ በስፍራው ከመድረሱ በፊት የአሸባሪው ሸኔ ቡድን በአካባቢው ማኅበረሠብ ላይ ከፍተኛ የሆነ ስቃይና እንግልት ያደርስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ሠራዊቱ ይህን የጥፋት ቡድን የመደምሰስ ግዳጅ ተቀብሎ ከአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ግዳጅ መፈፀም ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ በአምስት ወረዳዎች ጠላትን በመደምሠስ የአካባቢውን ሠላም መመለስ መቻሉ ተገልጿል።

የአሸባሪው የወያኔ ተላላኪ ክንፍ የሆነውን የሸኔ ቡድንን ለመደምሰስ በተደረገው የተጠናከረ ዘመቻ በምስራቅ ወለጋ ዞን በጋቲራ ቀበሌ ከህዝቡ ተዘርፈው የተወሰዱትን 40 የቀንድ ከብቶች ለባለቤቶቻቸው መመለሳቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡