የአባቶቻችን የአድዋው ድል በጉባ ተራሮች ግርጌ ተደግሟል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ነሐሴ 6/2014 (ዋልታ) የአባቶቻችን የአድዋው ድል በጉባ ተራሮች ግርጌ ተደግሟል ለዚህ ደግሞ አባይ ምስክር ነውሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሕዳሴ ግድቡ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

ትውልዳችን ታሪክን በደማቅ ቀለም ፅፏል፤ የረዳን ፈጣሪ ይመስገን ሲሉም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን የዘር፣ የሃይማኖት፣ የኢኮኖሚ ደረጃ እና የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድበን ከፍተኛ ዋጋ የከፈልንበት፤ በዓለም አደባባይ በፅናት የቆምንበት ታላቁ ህዳሴ ግድብ 3ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በድል ማጠናቀቅ በመቻላችን ይህቺ ቀን የድርብ ደስታችን ቀን ነች ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

ከተባበርን እንችላለን፤ ከተሳሰብን ይከናወንልናል፤ ከተደጋገፍን የብልፅግናን አቀበት በደስታ እንወጣዋለን ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ኢትዮጵያ በሀቀኛ ልጆቿ ጥረትና ትጋት ጨለማውን እየገፈፈች የብርሃን ዘመኗን ታዉጃለች ሲሉ በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የ3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግና የጀመረችውን ጉዞ ትቀጥላለች ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን ተናግረው፤ የኢትዮጵያዊነታችን አርማ የጋራ ጥረታችን አሻራ የሆነው ግድባችን 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት እውን ለሆነበት ለዚህ ታሪካዊ ቀን እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ፕሮጀክቱ ለስኬት እንዲበቃ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበትና በሀሳብ አሻራቸውን ማኖራቸውን አስታውሰው፤ “የልፋታችሁን ዋጋ እንኳን ለማየት አበቃችሁ” ማለታቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡