በሻምፒዮናው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበው አትሌቲክስ ልዑክ የሽልማት መርኃ ግብር ተካሄደ

ነሐሴ 7/2014 (ዋልታ) በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው የዓለም ከ20 በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን የዕውቅና እና የሽልማት መርኃ ግብር ተካሄደ።

በ19 አትሌቶች በ10 የውድድር ዓይነት ተሳትፎ ያደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ከዓለም 3ኛ ከአፍሪካ 1ኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወቃል።

በውድድር ሜዳሊያ ላስገኙ አትሌቶችና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ሽልማት ሲበረከት ወርቅ ሜዳሊያ እንዲመጣ ላደረጉ አትሌቶች 300ሺሕ ብር እንዲሁም የብር ሜዳሊያ ላስገኙ አሰልጣኞች 200ሺሕ ብር ተሸልሟል።

በውድድሩ የወርቅና የብር ሜዳሊያ ያስገኘው ኤርምያስ ግርማ የ500 ሺሕ ብር ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለአትሌቶቹ ሽልማት ያበረከት ሲሆን ወርቅ ሜዳሊያ ላገኙ አትሌቶች የ150 ሺሕ ብር ሽልማት አበርክቷል።

በሽልማት መርኃ ግብሩ የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሸገርን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በሚኪያስ ምትኩ