ኮሚሽኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

ነሐሴ 12/2014 (ዋልታ) የጉምሩክ ኮሚሽን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የኮሚሽን የማኔጅመንት አባላት በ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና በ2015 እቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል።

በኮሚሽኑ ባለፈው የበጀት ዓመት የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል እና ውስንነቶችንም ለመቅረፍ በአዲሱ የበጀት ዓመት የላቀ ርብርብ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በ2014 የበጀት ዓመት የሀገርን ኢኮኖሚ ያሳደጉ እና የሕዝብንም ደኅንነት ያስጠበቁ ሥራዎችን ኮሚሽኑ መስራቱን አስታውቀዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመትም 154 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 140.5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንም ጠቁመዋል።

በህግ ማስከበር ዘመቻ በተለይም ደግሞ የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ ፍሰትን በመከላከል እና በመቆጣጠር ኮሚሽኑ ባለፈው የበጀት ዓመት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡንም አስረድተዋል።

በዚህም 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢ እና የውጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን አስታውሰዋል።

ኮሚሽኑ ባለፈው የበጀት ዓመት በንግድ ማጨበርበር እና ኮንትሮባንድ መከላከል ዙሪያ የውስጥ አቅም፣ የኅብረተሰብ እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን በማጠናከር ሀገር ልታጣው የነበረውን ብር 50.4 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉንም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

በአዲሱ የበጀት ዓመትም ኮሚሽኑ በመንግሥት የተሰጠውን ተልእኮ ለመወጣት በሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራ እና ከአጋር አካላት ጋር የተጀመረው የትብብር ስምምነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በውይይቱ ማጠቃለያ መገለጹን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።