በብሔራዊ የጤና ፍትሃዊነት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው

ነሐሴ 12/2014 (ዋልታ) በብሔራዊ የጤና ፍትሃዊነት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡

የጤና ሚኒስቴር ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር “በተቀናጀ ጥረት የተፋጠነ የጤና ፍትሃዊነት ለጤናማ እና ፍትሃዊ ማኅበረሰብ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ነው መድረኩ እያካሄደ የሚገኘው።

የጤና ሚኒስቴር ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም በአምስት ዓመታት ውስጥ የሚተገበር ፍትሃዊ የጤና ተደራሽነት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርፆ ወደ ትግበራ መግባቱ ፍትሃዊ የጤና ተደራሽነት ላይ ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ አድርጓል ተብሏል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና አገልግሎት ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥና በሌሎችም ምክንያት መገደብ እንደሌለበት ዓለም አቀፍ ህግጋትን ጠቅሰው ገልፀዋል።

የጤና ፍትሃዊ ተደራሽነት ስትራቴጅክ እቅዱን በአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ እና ሌሎችም ዝቅተኛ አፈፃፀም ባለቸው አርብቶ አደሮች በሚገኙባቸው ዞኖችና ወረዳዎች ላይ ብቻ በልዩነት እየተተገበረ ነው ብለዋል።

የጤና ተቋማትን መገንባት፣ የአምቡላንስ ትግበራ እና ሌሎችም የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ሰፊና ውጤታማ ቢሰራም በቂ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

ዕቅዱን በመተግበር ሂደት ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ግጭትና የመሰረተ ልማት አለመሟላት ፈተና እንደሆኑ ተናግረዋል።

የጤና አገልግሎት ኢፍትሃዊነትን ለማጥበብም የሁሉም ሴክተሮች ቅንጅታዊ ሥራ ይጠይቃል እና ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።

በትዕግስት ዘላለም

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW