የክልሉ መንግሥት ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

ነሐሴ 12/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል መንግሥት ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሀረሪ ክልል ከሚገኙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሥራ ትውውቅ አድርጓል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላ በትውውወቅ መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርግ በመሆኑ ለውጤታማነቱ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥትም ለኮሚሽኑ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባል መላኩ ወልደማርያም ኮሚሽኑ በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት፣ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እንዲሁም ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት እገዛ ያበረክታል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መምከርን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመዋል።

ምክትል ኮሚሸነር አምባሳደር መሐመድ ድሪር በበኩላቸው በሀገሪቱ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በምክክር መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም ሁሉም በመተባበር የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ እውን ማድረግ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙ ከፍተኛ አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት ለኮሚሽኑ ውጤታማነት የበኩላቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት ገልፀዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW