በሀረሪ ክልል ነፃ የህክምናና የምርምራ አገልግሎት መሰጠት ተጀመረ

ነሐሴ 16/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል ነፃ የህክምናና የምርምራ አገልግሎት መሰጠት ተጀመረ፡፡

“በጎነት ለጤናችን” በሚል መሪ ቃል የሚሰጠው ነፃ የህክምናና የምርምር አገልግሎት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አስጀምረውታል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛል።

በእለቱ የተጀመረው አገልግሎትም መክፈል የማይችሉ ዜጎች በነፃ የህክምናና የምርመራ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

በቀጣይም መሰል ተግባራት በሌሎች ዘርፎችም ተጠናክረው ይቀጣሉ ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ እንደገለጹት የሚሰጠው ነፃ የምርመራና የህክምና አገልግሎት አቅመ ደካማ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ 5 ሺሕ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

ነፃ የህክምና አገልግሎቱ በበጎ ፍቃደኛ የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት የሚሰጥ ሲሆን አገልግሎቱም በክልሉ በሚገኙ 16 የመንግስትና በተመረጡ የግል ጤና ተቋማት ይሰጣል።

ተጨማሪ  ህክምናና ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ወደ ከፍተኛ የጤና ተቋማት በመላክ አገልግሎቱን እንዲያገኙ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

በክልሉ የሚገኘው ህዝብም ከነሐሴ 16 እስከ 21 ቀን 2014 ዓ.ም  በሚሰጠው አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሐረር ቅርንጫፍ)