ለመከላከያ ሠራዊት አባላት መኖሪያ ቤት ለማስገንባት የሚያስችል ስምምነት ተካሄደ

ነሐሴ 16/2014 (ዋልታ) የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ለመከላከያ ሠራዊት አባላት የጋራ መኖሪያ ቤት ለማስገንባት ከኦቪድ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር ስምምነት ተፈራረመ።

የግንባታ ውሉን የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሜጀር ጄኔራል ኩምሳ ሻንቆ እና የኦቪድ ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ ተፈራርመዋል።

የሚገነቡት ቤቶች ባለ ሦስት እና አራት መኝታ ሲሆኑ በ14 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቁም በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተጠቁሟል።

ቤቶቹም ባለ ሰባት ወለል 128 ቤቶች እና ባለ ዘጠኝ ወለሉ ደግሞ 120 ቤቶች መሆናቸው ተገልጾ ኩምካንግ አሉሚኒየም ፎርምወርክ በተባለ ቴክኖሎጂ እንደሚገነቡ ተነግሯል።

በአጠቃላይ 248 ቤቶች የሚገነቡ ሲሆን ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግባቸውም ተገልጿል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ዛሬ ከተፈጸመው ውሉ በተጨማሪ በአዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ እና ባሕርዳር ከተሞች ከ2100 ቤቶች በላይ በመገንባት ላይ መሆኑም ተገልጿል።

ፋውንዴሽኑ ከዚህ ቀደም በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለሠራዊት አባላት ማስተላለፉ ይታወቃል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW