ክልሉ የሲሚንቶ ግብይት መመሪያን ተግባራዊ ለማድረግ ግብረ ኃይል አቋቋመ

ነሐሴ 16/2014 (ዋልታ) የሐረሪ ክልል የሲሚንቶ ግብይትና ሥርጭት መመሪያ ቅንጅታዊ አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ ግብረ ኃይል አቋቋመ፡፡

በክልሉ ስራውን ተናቦ ለመስራት ቅንጅታዊ አሰራርን ተግባራዊ ባደረገ መልኩ መስራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኝቱ ነው ከተለያዩ የመንግስት መዋቅር አግባብነት ያላቸው አካላትን ያካተተ ግብረ ኃይል የተቋቋመው፡፡

በቀጣይ በክልሉ ለሚካሄዱ የመንግስት ፕሮጀክቶች ቅድሚያ የሚሰጥ ሲሆን ለግል አልሚዎችም ድጋፍ ይደረጋል ተብሏል።

የተቋቋመው ግብረ ኃይል የሲሚንቶ ግብይትና ሥርጭት መመሪያ ለታለመለት ዓላማ መዋሉንና በወጣለት ተመን መሰረት ግብይት እየተካሄደ ስለመሆኑ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በቀጣይ የግብይት ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎች ብቃት ያላቸው ወጣት ማህበራት በዚህ ስራ ላይ እንዲሳተፉ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የሲሚንቶ ግዢ የሚፈጽሙ አካላት ደረሰኝ ይዘው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም የተጠቆመ ሲሆን ይህንን በማያደርጉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።