ማዕከሉ በሕክምና ግብዓቶች ዕጥረት በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን አስታወቀ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) ለልብ ሕክምና በሚያስፈልጉ የሕክምና ግብዓቶች ዕጥረት ሳቢያ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል አስታወቀ።

ማዕከሉ በአሁኑ ጊዜ በአንድ ሦስተኛ አቅሙ ብቻ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።

በማዕከል የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ናሆም ስንታየሁ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ የተሟላ ሙያተኛ ቢኖረውም ለልብ ሕክምና በሚያስፈልጉ የሕክምና ዕቃዎች ዕጥረት የተነሳ የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም።

ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ለልብ ሕክምና አገልግሎት የሚያስፈልጉ የሕክምና ግብዓቶች ከውጭ የሚገቡ መሆናቸውን የጠቆሙ ኃላፊው፤ ማዕከሉ ቋሚ ገቢ ስለሌለው የሕክምና ግብዓቶቹን በሚፈለገው ልክ የማስገባት አቅም የለውም ብለዋል፡፤

በግብአት ዕጥረት የተነሳ ማዕከሉ በዓመት ለ500 ሕጻናት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህ ዓመት አገልግሎቱን ለ750 ሕጻናት ለመስጠት አቅዶ የነበረ ቢሆንም ይገኛሉ ተብለው የታሰቡ እገዛዎች ባለመገኘታው ዕቅዱ ሊሳካ አልቻለም ብለዋል።

ማዕከሉ እስካሁንም በአገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ከመንግሥት መስሪያ ቤቶችና ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚያገኘው እርዳታ የሚተዳደር በመሆኑ የፋይናንስ አቅም ውስንነት እንዳለበት ተናግረዋል።

ማዕከሉ በቋሚነት ገቢ የሚያገኝበት መንገድ ባይፈጠርም ከጤና ሚኒስቴር በርካታ ድጋፎችን እያገኘ መሆኑን ገልጸው፤ በቅርቡም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከሮተሪ ጋር የአራትዮሽ የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል። በዚህ ስምምነትም መሰረትም 100 ሕጻናት ወደ ውጭ አገር ሄደው ሕክምና እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

በየቀኑ ከአስር እስከ አስራ ሁለት የሚሆኑ ሕጻናት ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ‹‹በሪፈር›› ወደ ማዕከሉ ይመጣሉ ያሉት ኃላፊው፤ አሁን ላይ ሰባት ሺሕ 200 ሕጻናት ለሕክምናው ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

በየሳምንቱ ለሦስት ሕጻናት ሙሉ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና እንዲሁም ለስድስት ሕጻናት በደም ስር የሚሰጥ ‹‹ፕሮሲጀር›› ሕክምና በአጠቃላይ በሳምንት ለዘጠኝ ሕጻናት ነፃ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።