የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉ ተገለፀ

ነሐሴ 19 ቀን 2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያየ ምክንያት ተዘግተው የቆዩ ከ170 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ እድል መፍጠሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2015 ዓመት እቅድ ዙሪያ በሀዋሳ ከተማ ምክክር እያካሄደ ነው።

በዚህ ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንደገለጹት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክቱ ከ179 በላይ የተዘጉ ኢንደስትሪዎችን ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ሚናቸውን እንዲጫወቱ አድርጓል ብለዋል።

ለውጤቱ ከፌደራል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ አመራሩ የወሰደው ሃላፊነት ከፍተኛ መሆኑንና ኢንዱስትሪዎችን በባለቤትነት መምራቱን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በሌላ በኩል ዓመቱ የኤክስፖርት ምርትን በማሳደግ እንዲሁም የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትና በስራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።