ግዙፉ ዩኒሊቨር ኩባኒያ በኢትዮጵያ የምግብ ማቀነባበር ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ዩኒሊቨር የተባለ የአለማችን ግዙፍ ኩባኒያ በኢትዮጵያ የምግብ ማቀነባበር ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡

በለንደን የኢትዮጵያ መንግስት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ እና ኩባኒያው የአፍሪካ ኮርፖሬት ጉዳዮች ዳይሬክተር ዳጊ በሩ በምግብ ማቀነባበር ኢንቨስትመት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ተፈሪ፤ መንግስት ቅድሚያ በሰጠው የአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ የውጪ ባለሃብቶች በሚሰጠው ማበረታቻ ዩኒሊቨር ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸው፤ በምግብ ማቀነባበር ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ላቀረበው ጥያቄ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡

የዩኒሊቨር የአፍሪካ ኮርፖሬት ጉዳዮች ዳይሬክተር በበኩላቸው ላለፉት አመታት ኩባኒያቸው በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ የጽዳት ምርቶች፣ የተለያዩ ሳሙናዎችና ሻምፖዎች እንዲሀም ልዩ ልዩ ምርቶችን በማምረት ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራቱን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ በስፋት ለመንቀሳቀስ ፍላጎት እንዳው አስታውቀዋል፡፡

ዩኒሊቨር ለምርት የሚሆነውን ጥሬ ግብአት ከሀገር ውስጥ አርሶአደሮች በመግዛትና በሀገር ውስጥ በማምረት የሚገኘውን ትርፍ ሀብትም መልሶ በሀገር ውሰጥ ኢንቨስትመንት ላይ እያዋለ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይነትም ከሌሎች የውጪ ባለሃብቶች ጋር በመቀናጀትም ሆነ በተናጠል በኢትዮጵያ የምግብ ማቀነባበር ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረው በቅርቡም የኢንቨስትመንት እቅዳቸውን እንደሚያቀርቡ አመልክተዋል፡፡

ዩኒሊቨር በአለማችን ከ192 በላይ ሀገራት በተመሳሳይ የኢንቨስትመንት ስራ ላይ መሰማራቱን የኤምባሲው መረጃ ያሳያል፡፡