የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ገበያውን ማረጋጋት እንደተቻለ ተገለጸ

መላኩ አለበል

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ የገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ገበያውን ማረጋጋት መቻሉን አስታወቀ።

የኤክስፖርት አቅምን ለማሳደግ በተሰራው ሥራም ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ከ500 ሚሊዮን 44 ሺሕ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱም ተመላክቷል።

ሚኒስቴሩ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን በገመገመበት መድረክ የተገኙት ሚኒስትሩ መላኩ አለበል “በዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት ከዕቅድ አንጻር ውጤት ተገኝቶባቸዋል” ብለዋል።

ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚሆኑ የገቢ ምርቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ጥሬ እቃዎችና ኢንዱትሪዎች በመጠቀም ለማምረት የተሰራው ሥራ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸውን የገቢ ምርቶች በሃገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል ብለዋል፡፡

ይህም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት ከማሳደግ ባለፈ ገበያውን ለማረጋጋት ማስቻሉንም አመልክተዋል።

ሚኒስትሩ አንዳሉት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በመጨመርና ወደውጭ የሚልኳቸውን ምርቶች መጠን ከፍ በማድረግ የኤክስፖርት መጠኑን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ በሃገሪቱ የኤክስፖርት ታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ውጤት ተገኝቶበታል።

የተገኘው ውጤት ሀገር በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆና የተመዘገበ መሆኑን ጠቁመው ያጋጠሙ ችግሮች በኤክስፖርት መጠን እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ነበራቸው ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሻሻል ረገድ ሰፊ ሥራ ቢሰራም በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ያለው የግብዓት ችግር አሁንም ተግዳሮት መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 52 ከመቶ መድረሱን ገልጸው ይህንን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የዘርፉን ማነቆ በመፍታት ኤክስፖርትን ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪዎቹ ለዜጎች ጥራት ያለው የስራ እድል መፍጠራቸውንና ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲያከናውኑ በተደረገ ድጋፍ 74 ወደ ገበያ መግባት የሚችሉ ሃገር በቀል የምርምር ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለተከናወኑ ተግባራት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጉልህ ሚና መጫወቱን ጠቅሰው በየአካባቢው ያሉ ኢንዱስትሪዎቹ ባለቤት እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በኢንደስትሪዎች የሚታየውን የመሰረተ ልማት፣ የፋይናንስ፣ የግብዓት፣ የአደረጃጀትና የሰው ኃይል እጥረት መቅረፍ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከ179 በላይ በተለያየ ምክንያት የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በማስገባት በኢኮኖሚው ዘርፍ ሚናቸውን እንዲወጡ የንቅናቄ ድርሻ ከፍተኛ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!