የመኖሪያ ቤት ኪራይ መጨመርን የሚከለክል ደንብ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተራዘመ

ነሐሴ 20/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ኪራይ መጨመርም ይሁን ተከራይን ማስወጣት የሚከለክለው ደንብ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንዲራዘም ተወሰነ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን የኑሮ ጫናን ለመቀነስ በመኖሪያ ቤት ተከራዮች ላይ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ እና ተከራይን ማስለቀቅን የሚከለክል ደንብ አውጥቶ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ይህም ደንብ በተለያየ ጊዜ እየተራዘመ ላለፈው አንድ ዓመት ተግባራዊ ተደርጎ ቆይቷል፡፡

ስለሆነም የከተማ አስተዳደሩ አሁን ያለውን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ እና የኅብረተሰቡን የኑሮ ጫና ከግምት በማስገባት ወቅቱን በአብሮነትና በመተሳሰብ ለማለፍ ይረዳ ዘንድ ይህ ደንብ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንዲራዘም ወስኗል፡፡

በመሆኑም ይህንን ክለከላ በመተላለፍ ተከራዮችን የሚያስወጡ እና የኪራይ ዋጋን የሚጨምሩ አካላት ላይ ማኅበረሰቡ በሚከተሉት የስልክ ቁጥሮች ጥቆማውን ለከተማ አስተዳደሩ ማድረስ እንደሚችል አስታውቋል፡፡

የስልክ ቁጥሮቹም፦ አጭር ቁጥር ፡- 9977 ፣ የሞባይል ስልኮች 09-00640830 / 09-00640789 መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!