ሰላምን ባለመቀበል ጦርነት የከፈተውን አሸባሪ ቡድን የትግራይ ህዝብ ሊቃወመው እንደሚገባ ተገለፀ

ሱራፌል ጌታሁን

ነሐሴ 25/2014 (ዋልታ) የሰላም አማራጭን ባለመቀበል በተደጋጋሚ ጦርነት የከፈተውን አሸባሪው የሕወሓት ቡድንን የትግራይ ህዝብ በአንድነት ሊያወግዘውና ሊቃወመው ይገባል ሲሉ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ሱራፌል ጌታሁን ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁሩ አሸባሪው ሕወሓት የመንግስትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው በተደጋጋሚ ጦርነት ማወጁ የሰላም ፀር መሆኑንና ያለ ጦርነት መኖር እንደማይችል ያሳየበት ነው ብለዋል።

በዚህም የትግራይ ህዝብን መከራ ውስጥ እንዲቆይ እያደረገው መሆኑን ገልጸው በተለይም የትግራይ ክልል ህፃናት፣ ወጣቶችና አቅመ ደካሞችን ለሞትና የከፋ ችግር እየዳረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት የጀመረውን የሰላም አማራጭ በመተው አሸባሪው ሕወሓት የጥፋት ድርጊቱን በግልጽና በአደባባይ ያሳየበት እንደሆነ ነው ምሁሩ የገለጹት።

ቡድኑ ጦርነትን የህልውና ማስቀጠያ አድርጎ ስለሚወስድ ከጦርነት ውጪ ሌላ አማራጭ አይታየውም ሲሉ አስረድተዋል።

ቡድኑ እያደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ እያለፈ ይገኛል ብለዋል።

አሸባሪው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰላም ወዳድ በመምሰል የሚነዛው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማሳሳት በትግራይ ህዝብ ላይ መከራ እንዲበዛ እያደረገ መሆኑን ምሁሩ አመላክተዋል።

የፌዴራል መንግስት የዜጎች ደህንነትን ለመጠበቅ የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚደግፉ ያስታወቁት ምሁሩ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅበትን መወጣት አለበት ነው ያሉት።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!