ኢትዮ ቴሌኮም ለደንበኞቹ አዲስ አገልግሎት ይፋ አደረገ

ነሐሴ 26/2014 (ዋልታ) ኢትዮ ቴሌኮም የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ክፍያን በቴሌ ብር መፈፀም የሚያስችል አዲስ አሰራር ይፋ አደረገ።

የዲጂታል ኢትዮጵያን ሀሳብ  እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም በጥሬ ብር ይደረግ የነበረውን እንቅስቃሴ በቴሌብር ማድረጉ ጊዜና ወጪን ከመቆጠቡ ባሻገር ለተቋማት ጥቅሙ የጎላ እንደሆነ አስታውቋል።

 

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት እስካሁን ይሰጥ የነበረውን የጥሬ ገንዘብ አገልግሎት በቴሌ ብር አማካኝነት በማድረግ ደንበኛው ሰነዶችን በድረገፅ በመሙላት አገልግሎቱን የሚያቃልል አዲስ አገልግሎት ነው ይፋ የሆነው።

 

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልፀው ጊዜ ከመቆጠብ ባለፈ ያለንን ውስን ሀብት ተጠቅመን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንድናገኝ ያስችለናል ብለዋል።

 

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን በቀን ከ7ሺሕ 300 በላይ ደንበኛ እንደሚያስተናግዱ ገልፀው አሁን ላይ በኢትዮ ቴሌኮም ይፋ የተደረገው አዲስ አገልግሎት ለደንበኛው ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

 

ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የውል ስምምነት አድርገዋል።

በሱራፌል መንግስቴ