ሩሲያ ያዘጋጀችው ግዙፉ “ቮስቶክ 2022” የጦር ልምምድ መካሄድ ጀመረ

ቮስቶክ 2022 የጦር ልምምድ

ነሐሴ 26/2014 (ዋልታ) ሩሲያ፣ ቻይናና ህንድን ጨምሮ የ14 ሀገራት ወታደሮች የሚሳተፈውና በሩሲያ ግዛት የሚካሄደው የጦር ልምምድ መካሄድ ጀመረ፡፡

በሩሲያ አስተናጋጅነት የሚካሄደውና 50 ሺሕ ወታደሮች እና የተለያዩ ጦር መሳሪያዎች ይሳተፋሉ በተባለው ግዙፉ ቮስቶክ 2022 የጦር ልምምድ በዛሬው እለት በምስራቅ ሩሲያ ግዛት በይፋ መከፈቱን ሩሲያን ቱዴይን ጠቅሶ አልዐይን ዘግቧል።

ቮስቶክ 2022 የሚል መጠሪያ የተሰጠው ወታደራዊ ልምምዱ ከዛሬ ጀምሮ ለ7 ቀናት በሩቅ ምስራቅ ሩሲያ እና በጃፓን ባህር ላይ የሚካሄድ መሆኑም ተነግሯል።

ከ5 ሺሕ በላይ የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ በተባለው በዚህ ልምምድ ከጦር መሳሪያዎቹ መካከልም 140 የጦር አውሮፕላኖች እና 60 የጦር መርከቦች እንደሚገኙበት የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል።

በልምምዱ ላይም የሩሲያ አየር ወለድ ወታደሮች፣ የረጅም ርቀት ቦምብ ጣይ ጄቶች እንዲሁም የጦር ካርጎ አውሮፕላኖች ከሌሎች ሀገራት የጦር መሳሪያዎች ጋር በመሆን እንደሚሳተፍም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በዚህ የጦር ልምምድ ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ቻይና የአሁኑ የጦር ልምምድ ከወቅቱ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ጋር እንደማይገናኝ መግለጿ ይታወሳል።

ይህ የጋራ የጦርነት ልምምድ በሩሲያ እና ቻይና ድንበር አቅራቢያ ካቦራቭስክ በሚባል ስፍራ እንደሚካሄድ የሩሲያ መከላከያ መረጃ ያወጣው መረጃ ያስረዳል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW