በሱዳን “የአፍሪካ ሕዝቦች የወዳጅነት ቀን” ፌስቲቫል ተካሄደ

ነሐሴ 30/2014 (ዋልታ) “የአፍሪካ ህዝቦች የወዳጅነት ቀን” ፌስቲቫል በሱዳን ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ምክር ቤት ተዘጋጅቷል፡፡

በፌስቲቫሉ ተቀማጭነታቸዉን ካርቱም ያደረጉ የአፍሪካ ሀገራት ኤምባሲዎችና ዜጎቻቸው መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡

በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በሱዳን የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት የኢትዮጵያን ባሕላዊ ምግቦች፣ የቡና አፈላል ሥነ-ሥርዓትና ልዩልዩ ባሕላዊ ውዝዋዜዎች ለታዳሚዎች አቅርበዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም አማራጮች የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል።

በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በፊስቲቫሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አፍሪካውያን ያላቸውን ሰፊ የባሕል ሐብት ለማስተዋወቅ እና የእርስ በእርስ ትሥሥራቸውን ለማጐልበት የመድረኩ ጠቃሚነት የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያንና የሱዳንን ባሕላዊ ትሥሥርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙት ለማጠናከር የሱዳን የወዳጅነት ምክር-ቤት የሚያደርገውን ጥረትም አድንቀዋል፡፡

ከኤምባሲዉ ጋር በጋራ የተጀመሩ ሥራዎችና ትብብሮችም ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ፌስቲቫሉ የሁለቱን ሀገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር መልካም ዕድል መፍጠሩንም በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል።