በዛሬው የበጎ ፈቃድ ቀን በየካቲት 12 ሆስፒታል የደም ልገሳ መርሐ-ግብር መዘጋጀቱ ተገለጸ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ በዛሬው የበጎ ፈቃድ ቀን በየካቲት 12 ሆስፒታል የደም ልገሳ መርሐ ግብር መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አስታወቀ።

ዕለቱን በማስመልከት በየካቲት 12 ሆስፒታል በዋናነት ከተዘጋጀው መርሐ ግብር በተጨማሪ በአዲስ አበባ የተለያዩ አደባባዮች ማህበረሰቡ በነቂስ ወጥቶ የደም ልገሳ ተግባር እንዲያከናውን ዝግጅት መጠናቀቁን የባንኩ ምክትል ዳይሬክተር ሃብታሙ ታዬ ገልፀዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የበጎ ፈቃድ ቀንን በማስመልከት ይተገበራሉ ተብለው ሰፊ ዝግጀት ከተደረገባቸው ተግባራት መካከል የደም ልገሳ መርሐ-ግብር አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የደም ባንኮች እና የጤና ቢሮዎች ለስራው መሳካት ዝግጅት መጨረሳቸውን ገልጸዋል።

ዕለቱን ምክንያት በማደረግ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር የተውጣጡ አካላት በዕለቱ የሚካሄዱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሐ-ግብሮችን በዋናነት እንደሚያስተባብሩም ኃላፊው ተናግረዋል።

የበጎ ቀን ሲባል ትልቁ በጎነት የደም ልገሳ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ በደም እጥረት ምክንያት ህይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉ ሰዎችን በበጎ ፈቃድ ደም በመለገስ መታደግ እንደሚቻል ገልፀዋል።

በክረምቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ድንኳኖችን በመትከል በጎ ፈቃደኞች ደም እንዲለግሱ በተከናወነው ስራ ከ3ሺሕ በላይ ዩኒት ደም በክምችት ደረጃ መኖሩንም ኃላፊው ገልፀዋል።

ይሁንና አሁን ባለው ተጨባጭ የሃገራችን ሁኔታ የሚያስፈልገው የደም ከምችት ከፍተኛ እጥረት የሚታይበት መሆኑን ተናግረዋል።

የደም ክምችት እጥረቱ እንደየደም አይነቱ የሚለያይ ቢሆንም በደም ባንክ የደም እጥረት ሲያጋጥም በየሆስፒታሎች የደም ፍላጎት ስለሚጨምር በዚህ ፍጥነት አገልግሎት ማግኘት ያለባቸው ታካሚዎች አደጋ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

ለአብነት “ፕሌትሌት” የተሰኘው የደም አይነት የመቆያ ጊዜው አምስት ቀን ብቻ ሲሆን ያለው የደም ክምችት ለሁለት ቀን የሚያገለግል መሆኑን የሚገልፁት ኃላፊው፤ በየቀኑ የሚከናወን ደም የማሰባሰብ ስራ እጅግ ወሳኝ መሆኑን መናገራቸውን ኢብኮ ዘግቧል።

ጊዜው የትምህርት ተቋማት የተዘጉበት ወቅት በመሆኑም የደም እጥረቱን ለመቅረፍ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በጎነትን በማሰብ በአቅራቢያው በሚገኝ የደም ባንክ በመገኘት ደም እንዲለግስ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።