በሀረሪ ክልል የበጎ ፍቃድ ቀን ተከበረ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል “ጳጉሜን በመደመር በሚል መሪ ቃል” የበጎ ፍቃድ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ ውሏል።

በእለቱም ለአቅመ ደካማ ወገኖች የታደሱ ቤቶች የተመረቁ ሲሆን ለአረጋውያን እና አቅመ ደካማ ወገኖች የምግብና የንፅህና ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን የደም ልገሳ መርሃ ግብርም ተካሂዷል።

መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ባለፈው አመት በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት አመት ቢሆንም በአሸባሪውና ተላላኪው ህውሃት በከፈተው ጦርነት የሀገራችን ሰላም አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም አንድነታችንን ማጠናከርና በሀገር ላይ የተደቀነውን አደጋ መመከት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የእለት ተእለት ተግባር ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው በመርሃ ግብሩም ሀይማኖት፣ ዘርና ፆታን ሳንለይ ሁሉንም በበጎነት ስሜት ማገልገል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

መርሃ ግብሩ አብርነትን መቀራረብንና ወንድማማችነት ያጠናክራል ሲሉ ተናግረዋል።

የክልሉ የመግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሔኖክ ሙሉነህ በበኩላቸው በክልሉ “ጳጉሜን በመደመር” በሚል መሪ ቃል በሚከናወነው መርሃ ግብር የተለያዩ ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልፀዋል።

በእለቱ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ መግዥ የሚሆን 875 ሺህ ብር ቃል ተገብቷል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)