ቴድሮስ አድሃኖም ሃላፊነታቸውን ባልተገባ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ገለጹ

ጳጉሜ 2/2014 (ዋልታ) የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ሃላፊነታቸውን ባልተገባ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ተናገሩ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ የተሰጣቸውን አለም አቀፍ ሃላፊነት እየተወጡ አይደለም ሲሉ አምባሳደሯ መግለጻቸውን ሄልዝ ፖሊሲ የተሰኘ ድረ-ገጽ አስነብቧል።

ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚሰጧቸው አስተያየቶች ከሙያ ስነ-ምግባር ያፈነገጡ እና ስልጣናቸውን ያለ አግባብ እየተጠቀሙ መሆኑን የሚያመለክቱ ከመሆናቸውም በላይ ተንኳሽ መሆናቸውን አምባሳደሯ አንስተዋል።

አምባሳደር ሂሩት አክለውም “ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነገር የሚመለከቱበት መንገድ ከሙያው በእጅጉ የራቀ ነው” ብለውታል፡፡

“የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በመሰለ ግዙፍ ተቋም ውስጥ ትልቅ ሃላፊነት የያዘ ሰው የአለም ጤና ጉዳይ ሊያሳስበው ሲገባ ስለሆነ ቦታ ብቻ በማውራት መጠመዱ አሳፋሪና ለያዘው ሃላፊነት የማይመጥን ነው” ብለውታል።

“የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር” የሚል ትልቅ ሃላፊነት በመያዝ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኝ አንድ ቦታ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ የሚያሳፍርና ስልጣንን ለእኩይ አላማ የመጠቀም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡