ጳጉሜ 2/2014 (ዋልታ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የትብብር እንጂ የንትርክ መንስኤ ሊሆን እንደማይገባ ሱዳናዊያን ምሁራን ገለጹ።
በኢትዮጵያዊያን የጋራ ትብብርና ጥረት እየተገነባ ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኃይል ማመንጫነቱ ባለፈ ዋነኛ የቱሪስቶች መዳረሻ የሚሆን ነው።
የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በ1 ሺሕ 700 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ የሚንጣለለው ሐይቅ የዓሳ ምርትም የአካባቢው ውበትም ሆኖ እንደሚታይ እንዲሁም በሃይቁ ላይ የሚፈጠሩት ከ70 ያላነሱ ደሴቶች የቱሪስቶች መዳረሻ ሲሆኑ አካባቢው የበርካታ አእዋፋት፣ እንስሳትና የእፅዋት ማእከል ጭምር እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሱዳን ካርቱም ተቀማጭነቱን ያደረገው የአፍሪካ የአስተዳደር፣ ሰላምና ሽግግር ጥናት ማዕከል ዋና ፀሐፊ ማህሙድ ዘይንላብዲን (ዶ/ር) ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአኅጉራዊ የጋራ ተጠቃሚነት የላቀ ትርጉም የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ምሁሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተለይም ለሱዳን ህዝብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚኖረው ይሆናል።
በግብርናው ዘርፍ ሱዳናዊያን በዓመት ሦስት ወቅቶች እንዲያዘምሩ በሱዳን ከተሞች የሚደርሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅን ለመቀነስና በዋነኝነት ደግሞ የኤሌክትሪክ ኅይል ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው መሆኑን ያብራራሉ።
ከዚህ ባሻገር ግድቡ ለጎረቤትና እህትማማች አገሮች ሁለንተናዊ ትስስር መጠናከር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ማህሙድ የዓባይ ውሃ የተፋሰሱ አገራት የውጥረት ምክንያት ሳይሆን የልማትና የትብብር ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
አገራት በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው ከተንቀሳቀሱና የጋራ ተቋማዊ አደረጃጀት ከፈጠሩ የመልማት እድላቸው ሰፊ መሆኑን አስረድተዋል።
የናይል ኢኒሸቲቭና መሰል ተቋማት አገራቱን በአንድ ጥላ ስር በማሰባሰብ ሁሉም ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በዓባይ ጉዳይ አዋጩ መፍትሔ ምክንያታዊ፣ ፍትሃዊና ዘላቂነት ያለው የውሃ ሀብት አጠቃቅምን መተግበር መሆኑን ገልጸዋል።
የቀድሞ የሱዳን ሪፐብሊክ መስኖና ውሃ ሀብት ሚኒስትር ዑስማን አቱም (ዶ/ር) ዓባይ በኢትዮጵያ በጥልቅ ሸለቆዎች፣ ወደ ሱዳን እየፈሰሰ ሁለቱን አገራት ያስተሳሰረ ስጦታ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኅይል ማመንጫ፣ ሱዳን ደግሞ ለመስኖ ልማት የመጠቀም ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ገልጸው ይህን ሀብት በትብብር አልምቶ በጋራ መጠቀም ይቻላል ይላሉ።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃን በመያዝ ለሱዳንና ግብጽ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው ግድቡ በግብጹ አስዋን ግድብ በየዓመቱ የሚባክነውን ከ4 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ ከትነት የሚታደግ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የዓባይን ውሃ በአሌክትሪክና በሌላም አገልግሎት በመተባበር በስርዓት ማልማት ከተቻለ ለሦስቱም አገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚበቃ መሆኑን አመልክተዋል።
ምናልባትም በትብብር መራመድ ከተቻለ በ2040 ምስራቃዊ ናይል ምጣኔ ሀብታዊ ዞንን መገንባት እንደሚቻል ገልጸዋል።
ሶስት አገራት ለሌላው ዓለም የሚተርፉበት ወርቃማ ዕድል እንዳላቸው ገልጸው ይህም ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ ምጣኔ ሀብታዊ ግንባታ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ፖለቲካዊ መልክ እየተሰጠው እንደሆነ ገልፀው በተለይም በግብጽ በማንም አካል ዓባይ ውሃ ከተነካ ተጎጂ ነኝ የሚል አቅም የተዛባ አቋም መያዟን ተናግረዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት የሚጠቀም እንጂ የዓባይን ውሃ የሚያስቆም ግድብ ባለመሆኑ፤አገራት ከተባበሩ ማንም ሳይጎዳ ይልቁኑም ሁሉንም ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት።
ሦስቱም አገራት ከስምምነት ለመድረስ መፍትሄው ውጫዊ ሦስተኛ ወገን መሻት ሳይሆን የመፍትሄ አካል ቁርጠኛ ሆኖ እርስ በርስ መነጋገርና ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋቸዋልም ብለዋል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!