ጳጉሜ 3/2014 (ዋልታ) “ሠላማችንን የሚነጥቁንና ወደ ግጭት እንድንገባ የሚያደርጉንን አካላት አጥብቀን እንቃወማለን” ሲሉ የሰላም ቀንን በማስመልከት ህዝባዊ ሰልፍ እያካሄዱ ያሉ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
በከተማዋ ‘ሰላም ለኢትዮጵያ’ በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያን የሠላም ፍላጎት የሚያንፀባርቅ እና አሸባሪው ህወሃትን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው፡፡
ሰልፈኛቹ “ኢትዮጵያ ሠላም ትፈልጋለች፣ ሠላም ለኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ነገም ታሸንፋለች፣ ሠላማችንን የሚነጥቁንና ወደ ግጭት እንድንገባ የሚያደርጉንን አካላት አጥብቀን እንቃወማለን” የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን እያሰሙ ነው።
በህዝባዊ ሰልፉ ላይ የኢትዮጵያውያንን የሠላም ፍላጎት ዝግጁነት የሚገልፁ እንዲሁም የአሸባሪውን ቡድን እኩይ ተግባር የሚያወግዙ መልእክቶች እየተላለፉ ነው።
በህባዊ ሰልፉ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞና በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብርሀም ማርሻሎን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡