ኢትዮጵያና ጅቡቲ ድንበራቸውን ከሽብርና ከሌሎች ወንጀሎች ለማጽዳት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አስታወቁ

ጳጉሜ 3/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያና ጅቡቲ ድንበራቸውን ከየትኛውም የሽብር እና ከሌሎች የወንጀል ተግባራት የማጽዳት ሥራ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አዲሱን የጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ዳይሬክተር ጄነራል ኮሎኔል አብዱረህማን አሊ ጋር ተወያይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ከዚህ ቀደም ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

በዚሁ መሠረት የሁለቱ ሀገራት ፖሊስ ተቋማት የጋራ የፀጥታ ግብረ ኃይል በማቋቋም በድንበር አካባቢ የጋራ ጥበቃ በማድረግ የጀመሩትን ተግባራት ገምግመዋል፡፡ እስከአሁን የተገኙ ውጤቶችን አጠናክረው ለማስቀጠልም ተስማምተዋል።

በሁለቱ ሀገራት የወንጀል ተግባር ፈጽመው የሚሸሸጉ ተጠርጣሪዎችን ለፈላጊው ሀገር አንዱ ለአንዱ አሳልፎ ለመስጠት የተጠናከረ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በውይይታቸው ወቅት አንስተዋል።

ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር (የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ) ላይ በወሰዱት እርምጃ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱንና ይህንን የወንጀል መከላከል ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት።