የተሻለ ዓለም ፣ ሀገርና ክልል ለመፍጠር ሰላም ቁልፍ መሳሪያ እነደሆነ ተገለጸ

ጳጉሜ 3/2014 (ዋልታ) የሰላም ቀን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በበቦንጋ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

‘ሰላም ለኢትዮጵያ’ በሚል መሪ በተከናወነ መርሃ ግብር “ለሠላም እሮጣለዉ” በሚል መሪ ቃል የ10ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተሻለ ዓለም፣ ሀገርና ክልል ለመፍጠር ሰላም ቁልፍ መሳሪያ እነደሆነ ተገለጿል፡፡

የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ምትኩ ባሹ እንደገለፁት ሰላም ወዳዱ መንግሥት ያስቀመጠውን የሰላም አማራጭ አሸባሪው ህወሓት ወደ ጎን በመተው ወደ ጦርነት በገባበት ወቅት ይህ ቀን መከበሩ የተለየ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡

የከፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዳሻዉ ከበደ  በመክፈቻ ንግግራቸዉ  የሀገራችን ሰላም እንዲረጋገጥ ሁላችንም የበኩላቸውን መወጣት ይኖርብናል ብለው የዞኑ ህዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን በመሆን ጦርነቱ በድል እስኪጠናቀቅ ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን ፍላጎታችን ልማትና እድገት ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪዉ ፤ ለዚህ ስኬት ደግሞ ሰላም ዋነኛው መሰረት ነው ብለዋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አንድነት አሸናፊ በበኩላቸው የምናከብረዉ የሰላም ቀን የሰላምን ዋጋ በትንሹ አዉስተን፣ ሰላም የየዕለት ሰላማዊ አስተሳሰብና ተግባር ዉህድ ውጤት መሆኑን ተገንዝበን ሁላችንም የሰላም ደቀ መ ዝሙር መሆን አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሰላም የሚመኝ ማንኛዉም ግለሰብ የራሱን፣ የቤተሰቡንና የህብረተሰቡን ሰላም በማስጠበቅ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የመንግሥት ተጠሪ ፀጋዬ ማሞ እንደገለፁት ቦንጋ ከተማ ላይ ቆመን ሰላምን መስበክ እንድንችል ያደረገን ምክንያት ከተማዋ ለሌሎች አከባቢዎች የሰላም ተምሳሌት በመሆኗ ነው በማለት አሁንም ህዝቡ ሰላሙን ይጠብቅ ዘንድ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የካፋ ዞን እያደረገ ያለውን ደጀንነት አመስግነው በትላንትናው ዕለት ብቻ 139 ሰንጋዎችና 26 በጎች ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

በጎዳና ላይ ሩጫ በወንድና በሴት በመሳተፍ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለወጡ አትሌቶች የማበረታቻ ሽልማት በክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተበርክቷል፡፡

በቦንጋ ከተማ የሰላም ቀንን አስመልክቶ የሰላም ፖል በክልሉ እና በዞኑ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መተከሉን የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።

በመርሃ ግብሩ ላ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች ተሳትፈዋል።