ጳጉሜ 4/2014 (ዋልታ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለጎረቤት አገራትም የብርሃን ምንጭ በመሆኑ እንደ ፕሮጀክት ባለቤት እንደግፈዋለን ሲሉ ግድቡን የጎበኙ የኬኒያና ደቡብ ሱዳን ልዑክ አባላት ተናገሩ።
የቀድሞ የናይሮቢ ከተማ ከንቲባና የኬኒያ-ኢትዮጵያ ወዳጆች ማኅበር ሊቀመንበር ጆ አኬች እና የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ወጣቶች ኅብረት ዋና ፀሐፊ ጀስቲን ኡሪዮ አጅንጎ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከጎበኘው የናይል ተፋሰሱ አገራት ልዑክ አባላት መካከል ናቸው።
“ግድቡን ለማየት በመታደሌ ፈጣሪን አመሰግናለሁ’ ያሉት ጆ አኬች፤ የሕዳሴ ግድቡን ኢትዮጵያ ብትገነባውም ፋይዳው ከኢትዮጵያ ባሻገር ቀጠና አቀፍ በመሆኑ የአፍሪካዊያን ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ለአብነትም ኬኒያና ኢትዮጵያ የኃይል ሽያጭ ስምምነቶችን ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው አገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ትስስር የሚበጅ እንደሆነ ገልጸዋል።
ስቲን ኡሪዮ አጅንጎ በበኩሉ ግድቡ የቀጣናውን አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ ሀብት መሆኑንና ጨለማ ውስጥ ላለችው አፍሪካ ብርሃን የሚፈነጥቅ ፕሮጀክት ነው ይላል።
ደቡብ ሱዳን ካላት መሬት 90 በመቶው የሚሆነው ለግብርና ስራ ምቹ መሆኑን ጠቅሶ፤ አሌክትሪክ ኃይል ካገኘች ያላትን ለም መሬት በመስኖ በማልማት “የአፍሪካ ዩክሬን” መሆን ትችላለች ነው ያለው።
እንደ ኬኒያ ሁሉ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ የኃይል ሽያጭ ስምምነት ማድረጋቸውን አስታውሶ፤ ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሁሉም የቀጣናው አገራት ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ባለቤቶቹ ሁላችንም ነን ብሏል።
ግድቡ ከየትኛውም ዓለም አቀፍ የገንዝብ ተቋም ድጋፍ ተደርጎለት ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ሀብት የሚገነቡት መሆኑ ደግሞ ለአፍሪካዊያን ተምሳሌት እንደሚያደርገው ነው የገለጹት፡፡
ግድቡ ሌሎች የተፋሰሱ አገራት በራሳችው አቅም መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚችሉ መነሳሳትን የሚፈጥር እንደሆነ ጆ አኬች ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ጀስቲን ኡሪዮ በበኩሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ካለው ቀጣናዊ ፋይዳ እንጻር፤ ለተፋሰሱ አገራት የድጋፍ ጥሪ ከቀረበ የደቡብ ሱዳን ወጣቶች የአቅማችንን በማዋጣት ግድቡ እስኪጠናቀቅ የማገዝ ፍላጎት አለን ብሏል።