የዘመን መለወጫ በዓል በለንደን ተከበረ

መስከረም 1/2015 (ዋልታ) በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑ ከ1 ሺሕ 500 በላይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አዲሱን የኢትዮጵያዊያንን ዘመን መለወጫ በዓል ለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ጊቢ ውስጥ አክብረዋል፡፡
ንግስት ኤልሳቤት ሁለተኛ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ማዘናቸውን የገለጹት ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ንግስቲቱ የኢትዮጵያና የዩናይትድ ኪንግደምን ግንኙነት ለማጠናከር የተጫወቱትን ሚና አስታውሰው ለንጉሳዊያን ቤተሰቦችና ለዩናይትድ ኪንግደም ህዝብ ሀዘኑ የጋራቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ከክፍለ ዘመን በላይ የቆየው ግንኙነት በሁሉም መስክ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢትዮጵያዊያኑ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ከምንጊዜውም በላይ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ለንጉሳዊያን ቤተሰቦችና ለመላው የዩናይትድ ኪንግደም መንግስትና ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
አምባሳደር ተፈሪ አክለውም በዓሉን ስናከብር አንድነታችንን ይበልጥ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በማትኮር ኢትዮጵያ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ የበኩላችንን ድጋፍ አጠናክረን በመቀጠል ሊሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡
በዛሬው የዘመን መለወጫ በዓል ላይ ያየነው አንድነታችን ኢትዮጵያዊያንን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ያኮራ፤ በተቃራኒው ደግሞ ከውስጥና ከውጪ ሆነው የሀገራችንን ውድቀት የሚመኙትን ያሳፈረ መሆኑን ተናግረዋል፡።
በዓሉ ሽብርተኛው ህወሓት በከፈተው ጥቃት ምክንያት በአማራና በአፋር ክልል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሰን በተሻለ ሁኔታ ለመገንባት የተያዘው እቅድ እንዲሳካ ገቢ የምናሰባስብበት አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው ከዚህ ቀደም ለጤና ተቋማት ግንባታ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
በቀጣይ ተመሳሳይ ዝግጅቶችን በማድረግ በአማራና አፋር ክልል ለወደሙ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በመላው ዩናይትድ ኪንግደም የገንዘብ ድጋፍ የማሰባሰቡ ስራ እንደሚቀጥል መናገራቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመለክታል።