አዲስ ዓመት እውነተኛ ተስፋ ያለው፣ ለመለወጥና ለመስተካከል በወሰንንበት አመለካከትና ልምምድ የሚከሰት ነው – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

መስከረም 1/2015 (ዋልታ) አዲስ ዓመት እውነተኛ ተስፋ ያለው፣ ለመለወጥና ለመስተካከል በወሰንንበት አመለካከትና ልምምድ የሚከሰት ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ አዲስ ዓመትን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ሙሉ መልዕክታቸው እንደሚከተለው ቀርቧል፦

እንኳን ለ2015 ዓ/ም አዲስ ዓመት አደረሰን፣ አደረሳችሁ፡፡

በተለምዶ የአሮጌውን ዓመት መሸኛና በአዲስ ዓመት መቀበያ ወቅት፣ ለወዳጅ ዘመድና ለወገን የመልካም ምኞት መልእክት ማስተላለፍ ተገቢ ነው፡፡

በአንፃሩ፣ በዚህ አዲስ ዓመት ተስፋና ምኞታችንን እውን እንዳይሆን፣ የትውልድ ትስስርና በብርታትና ጥንካሬ የመቀጠልና የመለወጥ ዕድል አመድ ከሚያለብሱ ደንቃራ ልምምዶች፣ አመለካከቶች እና አስተምህሮቶች በአርኣያ-ሰብ ሆነ በወኔያም አስተሳሰብና ድርጊቶቻችን የሚገለጹ (passionate manifests of thinking and actions) አትጊዎችን ለመቀየር አናመንታ።

የአዲስ ዓመት እውነተኛ ተስፋ ያለው፣ ለመለወጥና ለመስተካከል በወሰንበት አመለካከትና ልምምድ የሚከሰት ነውና።

ውድ ኢትዮጵያውያን፡-

እነሆ አገራችን የማትፈልገው ሆኖም መቋጫ ልታበጅለት ወደሚገባት ሶሰተኛ ዙር ጦርነት ተጎትታ ገብታለች። በዚህ ትውልድ በላ ጦርነት፣ ታሪክና የህዝባችንን የአንድነትና አብሮነት ጥንካሬ ማስያዣ አድርገው፣ ፈራሽ የፖለቲካ ቁማር ውስጥ የገቡ ሀይሎችን እና የከንቱ ውዳሴ ልክፍተኞችን በማስቆም፣ የአሮጌው አመት ጉስቁልናና መከራ ውጣ፣ የአዲሱ አመት ተስፋችንም ግባ የምንልበት የመልካም ምኞት ተማጽኖኣችንም መግለጫችንም ነው ።

ይህ ትውልድ ግዙፍ ተግዳሮቶች የገጠሙት ትውልድ ነው። ከተግዳሮቶቹ በላይ ሊያቆሙት የሚችሉትና ሊያሻግሩት የሚችሉት እሴቶች በህወሓት ድንክ ቁመና እና ቅንጭር ተክለ አስተሳሰብ ውስጥ የሉም።

በህወሓት ልክ መኖርና በህወሓት ስምሪት መነሁለል ለዚህ ትውልድ ስድብ ነው። እሳቤዎቹ ሰላም የላቸውም፤ ጥርጣሬና አለመተማመን የሚዘሩ፤ ፈሪነትን ፣ከንቱ የራስ ውዳሴን ፣ ባዶ ራስ አምላኪነትን፣ ስደትን ፣ ቸነፈርን፣ ጦርነትን ፣ መከራን እና ርሀብን ጠሪ ናቸው።

ስነ-ቃሎቹ ድባባቸው ከንቱ እና ባዶ፣ አንዱን ምርጥና የበላይ፣ ሌላውን የኮሰሰ እና የበታች አድርገው የሚያቀርቡ ደካማ እና ክፉኛ የበታችነት ስሜት ወይም ያለ ልክ የተንጠራሩ ልክፍታዊ ንባቦች የተጠናወታቸው አመት መጥቶ አመት ቢወጣ ሰውን በበጎ የማይቀይሩ የድሮ ድሪቶዎች ናቸው።

ህወሓት በጎልማሳ ሰው እድሜ ዘመኑ እሁንም ሰው በላ ጦርነትን በብዙ ንጹሀን ህጻናት መስዋእትነት ቁጥር ማነስና መብዛት ዘና ብሎ እንዲተነትንልን መፍቀድ የለብንም። ድል አድራጊነት አገርን ከጥቃት መከላከልና አንድነትን ማጽናት የትውልዳችን ድርብ ሀላፊነት እንጂ ብቸኛ ተልእኮአችን ከቶውንም አይደለም። ከዚህ ተልእኮ ባሻገር ህዝባችን የሞት የመከራ ጉስቁልና እና ስደት ፈረሶች የሆኑትን ሀይላት ሊያስቆማቸው ይገባል።

ህወሓት የነዚህ ሀይላት አውራ ነው። ከእጁ መከራ እየተቀበለ ያለው ህዝባችን ሳር ቅጠሉ ሁሉ ሳይቀር የማይቀበለው (ታክቲካዊ ቁማርተኞችን ሳይጨምር ) የመከራ ፈረስ ነው ። ህወሓት ኢ-ፍትሀዊ ልምምድን ለማስቀጠል የሚጥር አድሀሪ ህልመኛ ሀይል (reactionary force) ነው። ከዚህም በላይ ጎልምሶ አሁናዊ ቁመናው ከዚህም በላይ የከፋ ነው።

አስተምህሮታቸው በሉላዊ የእድገት አቅጣጫዎች እይታ ሚዛን የማይደፋ ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ በጎ እሴት የማይጨምሩ ይልቁንም ተስፋውን የሚያጠፋ ግራ እና ድርቅ የጉስቁልና ቀመሮች ናቸው። ሌሎች ለግዜው በህወሓት አስተምህሮት መስመር የቆሙትም ከእጁ መከራና ክህደት የቀመሱ በህወሓት የመዳረሻ ፍላጎት ላይ የጎላ ልዩነት የሌላቸው ሌሎች ድንክ የመከራ ፈረሶች ናቸው።

ልምምዶቻቸው ጨቋኝና ቤቶችን ያፈረሰ፤ ድንቁርናና መሀይምነት ዘረኝነትና ጥላቻን ያቀባበለ እና ሰንገው የያዙንን ማህበረ-ፓለቲካና ማህበረ-ኢኮኖሚ ችግሮች ያጠነከረ በአመዛኙ በችግር የተተበተበ አሳሪ ልምምድ ነው። አመለካከቶቻችንም ቢሆን በቅጡ ፍተሻ የሚሹ በጠላቶቻችን ፍላጎት እና የመጨረሻ ግብ ያልተቃኙና ያልተቋጠሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባናል።

የአሮጌው አመት ምንቸት ሲወጣ፤ ህወሓታዊ የአስተሳሰብ ድንክነትንና ቅንጨራን፣ ጦርነት ጎሳሚ፣ ስልብና ብርጉግ ስብእናን ጠርጎ እንዲወጣና፤ በጎ አዲሰ ልምምድ የወንዜ ጤናማ አቅል የሚያስገዛ ትምህርትን በእዝነ ልቡና የሚያሰርጽና ሰላምን የሚያረጋግጥ የእውነተኛ ጀግንነት እሳቤ ምንቸት ይግባ በማለት ነው።

ክብር ለጀግናው የመከላከያ ስራዊታችን!

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆችዋ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር።

ፈጣሪ ህዝባችንና ሃገራችንን ይባርክ!!

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!