የጸጥታው ምክር ቤት ሳምንት ባለሞላ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመወያየት የጠራው ስብሰባ ለሁለተኛ ጊዜ ውድቅ ሆነ

መስከረም 3/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ሳምንት ባለሞላ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመወያየት የጠራው ስብሰባ ለሁለተኛ ጊዜ ውድቅ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ታዬ ከኢኤምኤስ ጋር ባደረጉት ቆይታ የጸጥታ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ላይ ሊያደርገው ስላሰበው ስብሰባና ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ግልጽ ስብሰባ እንዲደረግ በተለይ አንዳንድ አውሮፓዊያን ሀገራት ለወቅቱ የጸጥታው ምክር ቤት ሰብሳቢ (ፈረንሳይ) ጥያቄ ባቀረቡት መሰረት ስብሰባው ሊካሄድ መታሰቡን አምባሳደር ታዬ ገልጸዋል፡፡
በሌላም በኩል አፍሪካዊያን እና ሌሎች ሀገራት ደግሞ የኢትዮጵያን ጉዳይ የአሰራር ሂደትን ተከትሎ ማጣራት እንጂ በቀጥታ ፎርማል ስብሰባ ማድረግ አያስፈልግም የሚል አቋም መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች መስማማት ባለመቻላቸው ጳጉሜ 3 ቀን 2014 እንዲሁም መስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም ሊደረግ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ስብሰባ አለመሳካቱን ነው አምባሳደር ታዬ የጠቆሙት፡፡
ምክር ቤቱ ከኅዳር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የሕዳሴ ግድብን ሳይጨምር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለ12 ጊዜ ያህል ስብሰባ መጥራቱን እና ሁለት ጊዜ መግለጫ ማውጣቱን ያስታወሱት አምባሳደር ታዬ ኢትዮጵያ የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ አይደለችም ብለዋል፡፡
ከራሳቸው ፍላጎት በመነሳት የኢትዮጵያ ደመኛ የሆነን ኃይል እንደማደጎ ልጅ የሚቆጥሩ አንዳንድ ሀገራት ደመኛው ሀይል ባለቀሰ ቁጥር ፋይል ይዘው ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ስለሚሮጡ ነው የኢትዮጵያ ጉዳይ በጸጥታው ምክር ቤት የሚታየው እንጂ የኢትዮጵያ ጉዳይ በምክር ቤቱ ሊታይ የሚገባው ሆኖ አይደለም ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በጸጥታው ምክር እስካሁን በተደረጉ ስብሰባዎች ሁለት ጊዜ መግለጫ ከማውጣት በስተቀር በኢትዮጵያ ላይ የተላለፈ ውሳኔ እንደሌለም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያም ‘የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ የውስጥ ጉዳያችን እንጂ የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ባለመሆኑ በራሳችን እንፈታዋለን’ የሚል አቋም ይዛ መዝለቋም አምባሳደሩ አስምረውበታል፡፡
በተባበሩት መንግስታት በአቅራቢያ ወይም በተዛማጅነት መርህ መሰረት ሀገራት ችግር ሲገጥማቸው ጉዳያቸው ወደ መንግስታቱ ድርጅት ከመምጣቱ በፊት በክፍለ አህጉር ድርጅቶች እንዲታይ ይደረጋል፡፡
በዚሁ አሰራር መሰረት ኢትዮጵያ የገጠማት የውስጥ ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ከመሄዱ በፊት በመጀመሪያ መታየት ያለበት በአፍሪካ ህብረት መሆኑን አምሳደር ታዬ አብራርተዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት እና በአፍሪካ ህብረት መካከል ያለው ግንኙነት መቃኘት ያለበትም በዚሁ መልኩ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በነስረዲን ኑሩ