መስከረም 4/2014 (ዋልታ) በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተማሪዎችንና የመምህራንን አቅም የሚያሳድግ የነጻ የትምህርት እድል ስምምነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በቻይና ኤምባሲ መካከል ተፈረመ፡፡
ስምምነቱ የኢትዮጵያን እና የቻይናን የቆየ ወዳጅነት እንደሚያጠናክር የተገለጸ ሲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት እመቤት ሙሉጌታ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ሼን ቂንሚን ተፈራርመውታል።
ምክትል አምባሳደሩ የነጻ የትምህርት እድሉ የተመቻቸው በቻይና መንግስት መሆኑን ገልጸው ይህም የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ያሳድገዋል ብለዋል፡፡
የነጻ የትምህርት እድሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ተማሪዎችና መምህራን ላላቸው እምቅ አቅም እውቅና ለመስጠትና የበለጠ እንዲያዳብሩት ለማስቻል ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት እመቤት ሙሉጌታ (ዶ/ር) በበኩላቸው የትምህርት እድሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ትርጉም ያለውና ለኅብረተሰቡ ጠቀሜታ ያላቸው በቴክኖሎጂ የተደገፉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል፡፡
ስምምነቱ መማር ላልቻሉ ተማሪዎች ድጋፍ በማድረግ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉና ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ ማስቻልም ሌላኛው ዓላማ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW