ፕሬዝዳንት አልሲሲ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዶሃ ገብተዋል

መስከረም 4/2015 (ዋልታ) የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ለሁለት ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ኳታር ዶሃ ገብተዋል።
ይህ የአልሲሲ ጉብኝት በፈረንጆቹ 2017 የገልፍ ሀገራት ኳታር ሽብርተኞችን ትረዳለች በሚል ማዕቀብ ከጣሉባት የፈረንጆቹ 2017 ወዲህ የመጀመሪያው ነው።
ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ አራት ሀገራት በኳታርና ላይ ማዕቀብ ሲጥሉ ግብጽም በይሁንታ ከተቀበሉ ሀገራት መካከል ነበረች።
አልሲሲ ትላንት ዶሃ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኳታሩ አሚር ሸይክ ታሚም ቢን ሐሚድ አልታኒ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች የሀገራቱን የሁለቲዮሽ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች እና በኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአውሮፓዊያኑ 2021 በኳታር ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ መነሳቱን ተከትሎ ኳታር ከአራቱ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያጠናክር ስምምነት ተፈራርማ እንደነበር የሚታውስ ነው።
ይህን ተከትሎም የሀገራቱ ግንኙነት የተሻሻለ ሲሆን የየሀገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተለያዩ ጊዜያት የእርስበርስ የስራ ጉብኝት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ግብጽ ያጋጠማትን የምጣኔ ሀብት ችግር በተለይም የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ያስችላት ዘንድ በነዳጅ ሀብት የበለጸጉ የአረብ ሀገራትን የማግባባት ስራ ስትሰራ የቆየች ሲሆን የአልሲሲ የዶሃ ጉብኝትም የዚሁ አካል ነው ተብሏል።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ከ50 በመቶ በላይ የስንዴ ፍጆታዋን ከዩክሬን የምታገኘው ግብጽ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተዳርጋ ቆይታለች።
ያለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የኳታሩ ግዙፍ የሀይድሮ ካርበን ኩባኒያ በግብጽ የ5 ቢልየን ኢንቨስትመንት ለማከናወን ማቀዱን ግብጽ አስታውቃም ነበር።
የኳታሩ አሚር አልታኒ በበኩላቸው በሰኔ ወር 2022 ግብጽን የጎበኙ ሲሆን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሀይልና እና ግብርናው ዘርፍ ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ መምከራቸውን አልጀዚራ አስነብቧል።
በአውሮፓዊያኑ 2013 አልሲሲ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን መጥተው የነበሩትን የቀድሞ የግብጽ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሙርሲን በሀይል ከስልጣን በማውረድ ስልጣን መቆናጠጣቸው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አሻክሮ እንደነበርም ይወሳል።
ከ350 ሺሕ በላይ ግብጻዊያን በኳታር በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን በየዓመቱ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዶላሮችን ወደ ሀገራቸው እንደሚልኩም ዘገባው አመላክቷል።
በነስረዲን ኑሩ