የምሥራቅ ባሌ ዞን ነዋሪዎች ከ10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ለመከላከያ ሰራዊት አደረጉ

መስከረም 6/2015 (ዋልታ) የምሥራቅ ባሌ ዞን ነዋሪዎች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው የአይነትና የስንቅ ድጋፍ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አድርገዋል።

የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር እየተዋደቁ ላሉት የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ደጀንነታቸውን እንደሚያጠናክሩም ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት፡፡

የዞኑን ወረዳዎች በማስተባበር 65 ሰንጋዎችና ከ1 ሺሕ የሚበልጡ ፍያሎችን ድጋፍ ማድርጉን የዞኑ አስተዳደር ገልጿል፡፡

በተጨማሪም በዞኑ የሴቶች አደረጃጀት የተዘጋጀ 254 ኩንታል የተለያየ አይነት ስንቅ እየተጓጓዘ መሆኑም ታውቋል፡፡

ከተዘጋጀው ስንቅ መካከል ዳቦ ቆሎ፣ በሶ፣ ድርቆሽ፣ ሩዝ፣ መኮረኒና ፓስታ ይጠቀሳሉ ሲል የገለጸው ኢዜአ ነው፡፡

የምሥራቅ ባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ መሐመድ ኢስማኤል እንዳሉት፤ ከዞኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለአገር ሉዓላዊነት መከበር በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት እየተደረገ የሚገኘው ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደቀጠለ ነው፡፡

በተያያዘ መረጃ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሸካ ዞን ለሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ያዘጋጀውን ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሰንጋዎችና በጎች ለመከላከያ ሚነስቴር አስረክቧል፡፡

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ ዘርሁን አንደሞ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደተናገሩት ለ3ኛ ጊዜ ተገደን የገባነውን ጦርነት በሁሉም ግንባሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ወረራውን እየመከተ ያለውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሎጀስቲክ መደገፍ አስፈላጊ ነው፡፡

በመሆኑም ዞኑ ነዋሪዎችን በማሳተፍ ያሰባሰባቸውን 60 ሰንጋዎች፣ 18 በጎችንና ፍየሎችን በአካል ቀርበን አስረክበናል ማለታቸውን የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።