መስከረም 7/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የገበያ ማረጋጋትና የገበያ አሻጥርን እየተከላከለ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የአስተዳደሩ የኢኮኖሚ አሻጥርና ኑሮ ውድነት መከላከል ግብረ ሀይል የዘመን መለወጫ የገበያ አቅርቦትን ገምግሟል።
በዚህም በዘመን መለወጫ የገበያ አቅርቦት እና የገበያ ዋጋ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከክልል አምራቾች፣ ከማህበራትና ከባዛር ጋር በማስተሳሰር በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ተደርጓል ብለዋል ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ።
በስኳር እና በሲሚንቶ ላይ የገበያ አሻጥር የፈፀሙ ግለሰቦች ላይም ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው በግምገማው ተገልጿል።
ካለፈው በዓል ተሞክሮ በመውሰድ መጪው የመስቀል እና የኢሬቻ በዓል ላይ በዓሉ የሚፈልገውን አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ከንቲባው አብራርተዋል።
በባለፈው የዘመን መለወጫ በዓል የምርት አቅርቦት ላይ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም፣ በመጪዎቹ በዓላት የምርት ዋጋን ለመቀነስ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።
የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ከተማ አስተዳደሩ በሪቮልቪንግ ፈንድ ለፍጆታ ምርቶች መግዣ 1 ቢሊዮን ብር መመደቡን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።