ሽንፈታችንን ተረድተን ወደ ኋላ ስናፈገፍግ በራሳችን ቡድኖች ስለምንገደል መማረኩን መርጠናል – ምርኮኞች

 

መስከረም 9/2014 (ዋልታ) ሽንፈታችንን ተረድተን ወደ ኋላ ስናፈገፍግ በራሳችን ቡድኖች ስለምንገደል መማረኩን መርጠን አጅ ሰጥተናል ሲሉ እጃቸውን ለመከላከያ ሰራዊት የሰጡ የአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎች ተናገሩ።

 

የሰራዊቱን ምት መቋቋም ባለመቻላቸው እጅ እየሰጡ መሆኑን የተናገሩት ምርኮኞቹ ወደ ኋላ እንዳይሸሹ የሽብር ቡድኑ የጥይት ሲሳይ እያደረጋቸው መሆኑንም ለዋልታ ተናግረዋል።

 

የአሸባሪው ሕወሓት አባላት እየደረሰባቸው ያለውን ምት መቋቋም ባለመቻላቸው በየግንባሩ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት እጅ እየሰጡ መማረካቸውን ገልጸዋል።

 

ከተማረክን በኋላ በጥምር ጦሩ እየተደረገልን ያለው እንክብካቤና ለቁስለኞች የተደረገው ህክምና አሸባሪው ህወሓት ከነገረን የተለየ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል።

 

ሲሸሽ ገደል ገብቶ እግሩ የተጎዳ አንድ ምርኮኛ እንደገለጸው 1 የራሱንና 1 የጓደኛውን በድምሩ 2 ክላሽ ለጥምር ጦሩ ማስረከቡን ተናግሯል።

 

በምዕራብ ግንባር ምርኮኞች ከነ መሳሪያቸው እጅ እየሰጡ ነው።

 

ተስፋዬ አባተ (ከምዕራብ ግንባር)