የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በዛሬው ዕለት መጀመሩን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

መስከረም 9/2015 (ዋልታ) የትምህርት ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በዛሬ ዕለት መጀመሩን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መጀመርን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት ተማሪዎች እና መምህራን እንዲሁም የትምህርቱ ማህበረሰብ እንኳን ለ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በሰላም አደረሳችሁ ብሏል።

ሁላችንም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ የበኩላችንን እንወጣ ሲልመ ነው መልዕክቱን ያስተላለፈው።

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ማስጀመሪያ መርሐግብር ተካሂዷል።

በትምህርት ማስጀመር ኘሮግራሙ የተገኙት ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ በአዲሱ አመት፣ በአዲስ ካሪኩለም መጀመሩን ገልፀዋል።

የተማረ አዕምሮ ተራራውን ሜዳ ያደርጋል ያሉት ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር፣ አሁን እየፈተን ያለው ሁኔታ የሚቀየረው ምክንያታዊ ትውልድ ሲፈጠር ብቻ ነው ብለዋል።

የአቃቂ ቃሊት ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አበራ ብሩ (ፒኤችዲ) በበኩላቸው፣ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በክፍለ ከተማው ባሉ 230 ትምህርት ቤቶች፣ 118 ሺህ በላይ ተማሪዎች ምዝገባ ተከናውኖ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።