የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በአላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ

መስከረም 9/2015 (ዋልታ) የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በአላት በሰላም እንዲጠናቀቁ በመሠረተ ልማትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በተቀናጀ አግባብ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለፀ።

በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በመዲናዋ የሚከበሩት ሁለቱ በአላት ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴትና ትውፊታቸው ተጠብቆ እንዲከበሩ ለማስቻል እስካሁን በሚመለከታቸው ተቋማት እየተደረገ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ተግባር ገምግመዋል።

በውይይቱ ላይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይልና ከአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት፣ ከመንገዶች ባለስልጣን፣ ከእሳት አደጋ፣ ከከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ፣ ከዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ፣ ከትራንስፖርት ቢሮ፣ ከፅዳት፣ ቄራዎችና ሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማት አመራሮች በየተቋማቸው የተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራ ያሉበትን ደረጃ በሪፖርት አቅርበዋል።

ዋና ስራ አስኪጁ በዚሁ ወቅት በአላቱ ያለ ምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከበሩ በአዲስ አመት አከባበር ወቅት የተከናወኑ ተግባራትን በመልካም ተሞክሮነት መውሰድ ይገባል ብለዋል።

አያይዘውም በቅርቡ ለሚከበሩት እነዚህ ህዝባዊና የአደባባይ በአላት የመብራት፣ የውሃ፣ የፅዳት፣ የእሳት አደጋ መከላከልና ሌሎች ለበአሉ አከባበር ወሳኝ የሆኑ አገልግሎቶች በተቀናጀ መንገድ በአፋጣኝ ሊፈፀሙ እንደሚገባም አሳስበዋል።

አክለውም በዚህ ቅንጅታዊ ተግባር መላው የከተማችንን ነዋሪዎች በማሳተፍና በማስተባበር እስከ በአላቱ ፍፃሜ ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አመልክተው የከተማው አስተዳደር ከፍተኛ አመራርም ተግባሩን በቅርብ ድጋፍና ክትትል መምራቱን እንደሚቀጥል ማስገንዘባቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ጠቁሟል።