የደቡብ ክልል 25ኛው የትምህርት አስተዳደር ጉባኤ በቡታጅራ እየተካሄደ ነው

መስከረም 10/2015 (ዋልታ) የደቡብ ክልል 25ኛው የትምህርት አስተዳደር ጉባኤው “ትምህርት ለሁሉም ሁሉም ለትምህርት” በሚል መሪ ቃል በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ብቁ ዜጎች ለማፍራት ታስቦ ትግበራው የተጀመረው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ስኬታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት በእዉቀትና በክህሎት የበቁ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ርዕሰ-መስተዳድሩ ጨምረው ገልጸዋል።

ባለፉት 30 ዓመታት በትምህርት ተደራሽነት ላይ ሰፊ ስራ መሰራቱን ነገር ግን በስነ ምግባር የታነፀና ብቃት ያለው ዜጋን በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ጉድለት እንደነበረበት በጥናት መለየቱንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ባለፉት ዓመታት ለተስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ጀምሯል ያሉት ርዕሰ-መስተዳድር ርስቱ ስራውም በአዲስ ስርዓተ-ትምህርት እንዲደገፍ አድርጓል ብለዋል።

በ2014 ዓ.ም በክልሉ በተወሰኑ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሙከራ ስራ መሰራቱን አስታውሰው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በአዲሱ የትምህርት ዘመን በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩንም ገልጸዋል።

ስለሆነም ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ስኬት ተገቢዉን ትኩረት ሰጥተዉ በመስራት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮው ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ፒኤችዲ) በበኩላቸው የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ትግበራ ዘላቂ ሀገራዊ አንድነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በክልል ደረጃ ሲዘጋጅ የነበረው ክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጅ ሲሆን ከዚህ ዓመት ጀምሮ በክልል ደረጃ የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እንደሚዘጋጅም አብራርተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች እና ሌሎእ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።