ኮሚሽኑ ያወጣው ሪፖርት ሞያዊ ግዴታዎችን ያላሟላና መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን የካደ ነው ተባለ

መስከረም 11/2015 (ዋልታ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ባለሞያዎች ኮሚሽን የወጣው ሪፓርት ሞያዊ ግዴታዎችን ያላሟላና መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን የካደ ነው ሲል በጄኔቫ የሚገኘው በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ከጅምሩም ኢትዮጵያ ኮሚሽኑ ጥናቱን እንዲያከናውን አመቺ ከባቢን መፍጠሯን አስታውሶ የኮሚሽኑ ባለሞያዎች የመስክ ምልከታ እንዲያደርጉ ጭምር ሁኔታዎች ተመቻችተው እንደነበር አስታውሰዋል።

ኮሚሽኑ ግን ይህንን ጥሪ ወደ ጎን በመተው እውነተኛ ያልሆነ ሪፖርት ከማውጣቱም በላይ የኮሚሽኑ ሪፖርት በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተመድ የሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር በጋራ ያወጡትን የምርመራ ውጤት ምክረ-ሃሳብ ያላከበረ ነው ብሏል።

የኮሚሽኑ ሪፖርት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ከማሳየት ይልቅ በሀገሪቱ ስጋት እንዲሰፍን የሚያደርግ እና ለሰላም እና እርቅ የተጀመሩ መንገዶችን ያላገናዘበ ነው ብሏል ጽህፈት ቤቱ።

በተጨማሪም ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ፖለቲካ ጫና በማጠናከር ሀገሪቱ ላይ ጫናዎች እንዲበረቱ የሚያደርግ እንደሆነም አስገንዝቧል።

መንግስት በሀገሪቱ ሰላም እና የሰብአዊ መብት እንዲከበር የጀመራቸውን ጥረቶች አስቀጥሎ ለመሄድ ቁርጠኛ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የተመድ የሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን  ያወጣውን ሪፖርት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ካውንስል በነገው እለት በኢትዮጵያ ጉዳይ ውይይት የሚያደርግ ይሆናል።