ሩሲያ እና ዩክሬን ከፍተኛ የሆነ የእስረኛ ልውውጥ ማድረጋቸው ተገለጸ

መስከረም 12/2015 (ዋልታ) ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከጀመሩ ከ7 ወራት ገደማ ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የእስረኛ ልውውጥ ማድረጋቸው ተገለጸ።

በጦርነት ውስጥ ያሉት ሁለቱ ሀገራት 300 ገደማ እስረኞችን መለዋወጣቸው የተገለጸ ሲሆን ሩሲያ ከለቀቀቻቸው የጦር እስረኞች መካከል ለዩክሬን ሲዋጉ የተያዙ እና በቅጥረኛ ተዋጊነታቸው የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበሩ የአሜሪካ፣ የብሪታኒያ እና የሞሮኮ ዜጎች ይገኙበታል ተብሏል።

በሩሲያ የተለቀቁት የውጭ ዜጎችም አምስት የብሪታኒያ፣ ሁለት የአሜሪካ፣ አንድ የሞሮኮ እና አንድ የስዊድን ዜጎች ሲሆኑ ሳዑዲ አረቢያ መግባታቸውም ታውቋል።

በተጨማሪም ሩሲያ በማሪፑል ውጊያ ላይ በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸውን 215 ዩክሬናዊያንን የለቀቀች ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አምስቱ ኮማንደሮች እንደሆኑም ተመላክቷል።

ዩክሬንም 55 ሩሲያዊያንን እና ለሩሲያ ወግነው ሲዋጉ የነበሩ ዩክሬናዊያንን የለቀቀች ሲሆን ከእነዚህም የሩሲያ ደጋፊ የሆነ ፓርቲ መሪ የሆነው እና በሀገር ክህደት ወንጀል ተከሶ የነበረው ቪክቶር ሜድቭድቼክ እንደሚገኙበት ሮይተርስን ጠቅሶ አልዐይን ዘግቧል።

የሩሲያ እና ዩክሬን የእስረኛ ልውውጥ ስምምነት በሳዑዲ አረቢያ እና በቱርክ አመቻችነት መፈጸሙ የተነገረ ሲሆን ስምምነቱ ለተወሰነ ጊዜ በዝግጅት ሂደት የቆየ እና ከፍተኛ ጭቅጭቅ ፈጠረ እንደነበር ተገልጿል።

ከዚህ ቀደምም በሳዑዲ አረቢያ ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን አሸማጋይነት 10 የውጭ ዜጎች ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።