መስከረም 12/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ደመራ እና የመስቀል በዓል እሴቱንና ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ህብረተሰቡ በትብብር እንዲሰራ ጠየቁ።
በአዲስ አበባ ከተማ ከመስቀል በዓል እና ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ህዝባዊ ውይይት ተደርጓል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓሉ ፀረ ሰላም ኃይሎች በጦርነት የደረሰባቸውን ኪሳራ በተላላኪዎቻቸው አማካኝነት አዲስ አበባ ላይ ለመመለስ ርብርብ በሚያደርጉበት ወቅት የሚከበር ነው ብለዋል።
እነዚህ ኃይሎች በዓለም ኢትዮጵያን ያስተዋወቁ በዓላት የስበት ማዕከል በመሆናቸው እንደ ትልቅ እድል ለመጠቀም እየሞከሩ መሆኑንም አንስተዋል።
ሆኖም ህዝቡ በየአካባቢው መፈናፈኛ እንዳሳጠቸው በመጥቀስ ክፍተት ካልተሰጣቸው ምንም አይነት መንገድ እንደሌላቸውም ገልጸዋል።
“ጦርነቱን ዳግም የምናሸንፋቸው በዓሉን ሰላማዊና ደማቅ አድርገን በማክበር ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች እነዚህ ሴረኞች ምንም እድል አይኖራቸውም” ብለዋል፡፡
“በእምነት በብሄር በአካባቢ እንደተከፋፈልን አስመስለው ለዓለም ማሳየት ለሚፈልጉ ኃይሎችም በዚህ በዓል አንድነታችንን ለዓለም እናሳያለን” ነው ያሉት።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ እሴቱንና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር እንደተዘጋጁ መናገራቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW