ኮሚሽኑ አሸባሪው ህወሓት በአፋር ከ107 ሺሕ በላይ ሰዎች ማፈናቀሉን ገለጸ

መስከረም 12/2015 (ዋልታ) አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ከ107 ሺሕ በላይ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር እና ምግብ ዋስትና ማተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ሃብት አሰባሳቢ እና ሎጀስቲክስ ኮሚቴ ከሀገራዊ የሃብት አሰባሳቢ እና ሎጀስቲክስ ኮሚቴ ጋር ባከናወናቸው ዐበይት ተግባራት ዙሪያ ዛሬ በሠመራ ከተማ ውይይት አድርገዋል።

ወረራውን ተከትሎ ክልሉ ባከናወናቸው ተግባራት ላይ ለመምከር በትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ የተመራ ልዑክ ሰመራ ይገኛል።

የህወሓት የሽብር ቡድን በክልሉ በተደጋጋሚ በፈጸመው ወረራ የከፋ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽነር መሐመድ ሁሴን ገልጸዋል።

ለችግር የተጋለጡት 107 ሺሕ 224 ሰዎች በዋናነት ከፈንቲ ረሱ ዞን ያሎ ጉሊና እንዲሁም ከኪልበቲ ረሱ ዞን መጋሌ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ሲሆን በአራት ጊዜያዊ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

ለእነዚህ ወገኖችም ከ7 ሺሕ ኩንታል በላይ የምግብ፣ ለእናቶች እና ሕፃናት ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ አልሚ ምግብ፣ የመጠጥ ውኃ በቦቴ ማቅረብን ጨምሮ ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሰብአዊ ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ተፈናቃዮቹ ባሉበት አካባቢ የሚገኙ ጤና ተቋማትን በግብአት እና የሰው ኃይል ለማጠናከር ተሞክሯል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በክልሉ ላይ በፈጠረው ችግር የተጎዱ ወገኖች በቀጣይ ለምግብ፣ ለመድኃኒት እና ተያያዥ ግብአቶች አቅርቦት የሚውል ከ107 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ አቶ መሐመድ ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ በበኩላቸው፤ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የአፋር ህዝብ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር መፈተኑን ተናግረዋል።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአፋር ህዝብ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ያሳየው ወገናዊ አጋርነት የመረዳዳት አኩሪ እሴታችንን ያደሰ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይም የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ በተደረገው ርብርብ የኢትዮጵውያን ትብብርና ህብረት እንደሚደነቅ አውስተዋል።

በዚህም የአፋር ክልልና ህዝብ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም የሽብር ቡድኑን የጥፋት ሴራ ለማክሸፍ የላቀ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል።