መስከረም 14/2015 (ዋልታ) የኢትዮ ቴሌኮም ምስራቅ ሪጅን ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ዲጂታል ቤተመጽሐፍ ገንብቶ አስረክቧል።
የሪጅኑ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ጣሰው ሽመልስ ዲጂታል ቤተመጻሕፍቱ ትውልዱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚረዳ ሲሆን ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ ለሚገኘው ኦዳ ቡልቱም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገነባ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቤተ መጻሕፍቱን ለማደራጀት 21 ኮምፒውተሮች ደረጃቸውን ከጠበቁ ጠረጴዛና ወንበሮች ጋር እንዲሁም ማተሚያ ማሽንና 11 ‘ሜጋ ባይት’ ፋይበር ኦፕቲክስ ኢንተርኔት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
እንደዳይሬክተሩ ገለጻ ቤተመጻሕፍቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት መስጠት የሚያስችል በመሆኑ ችግር ፈቺ ትውልድ ለማፍራት ጠቀሜታው ትልቅ ነው።
ከዲጂታል ቤተ መጻሕፍቱ በተጨማሪም ከ500 በላይ ደርዘን ደብተርና እስክርቢቶ በማቅረብ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎችን ማገዙን ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አወል አብደላ በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት ማደራጀቱ ተማሪዎች ከዓለም ጋር የሚገናኙበት መንገድ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ከ1 ሺሕ 500 በላይ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙም በማድረግ ብዙ ሸክም ማቅለሉን ጠቁመዋል፡፡